የበዓል ማስታወቂያዎች

ሐምሌ 17 ቀን 2008 ዓ. ም. (July 24 / 2016) የሚከበረውን ዓመታዊ የቅዱስ ገብርኤል በዓል ምክንያት በማድረግ በዋዜማው ቅዳሜ ሐምሌ 16 ቀን 2008 ዓ. ም. (July 23 / 2016) ከሰዓት በኋላ ጀምሮ በተጋባዥ መምህራንና ካህናት አባቶች ቤርሾዳለን 44 በሚገኘው ቤተ ክርስቲያናችን የሁለት ቀን መንፈሳዊ ጉባኤ ይደረጋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በዓሉ ሌሊቱን በማኅሌት፣ ጧት በቅዳሴ፣ በዝማሬ፣ በትምህርተ ወንጌልና በሥርዓተ ንግሥ የሚከበር ሲሆን በዕለቱ ሥርዓተ ጋብቻ የሚፈጽሙትን ሙሽሮች የተመለከተ ልዩ መንፈሳዊ መርሐ ግብር የሚኖር ይሆናል፡፡

ስለዚህ ይኸንን መንፈሳዊ መልእክት የምታደምጡ ወገኖች ሁሉ ካላይ በተጠቀሰው ቀንና ሰዓት በቦታው ተገኝታችሁ የጉባኤውና የዚህ ታላቅ መንፈሳዊ በዓል በረከት ተሳታፊ ትሆኑ ዘንድ በእግዚአብሔር ስም ተጋብዛችኋል፡፡

እንዲሁም ቅዱስ ገብርኤል በሚውልበት ዕለት ማለትም ሐምሌ 19 ቀን 2008 ዓ. ም. (July 26 / 2016) ማክሰኞ ጧት ከ8፡00 ሰዓት ጀምሮ የቅዳሴ መርሐ ግብር የሚኖር መሆኑን ከወዲሁ እንገልጻለን፡፡

እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡

Kidame Ehud

ቤተ ክርስቲያናችን አዲስ የሰበካ ጉባኤ አባላት ምርጫ አደረገች

ዛሬ ግንቦት 7፣ 2008 ቤተ ክርስቲያናችንን በአመራር የሚያገለግሉ አዳዲስ የሰበካ ጉባኤ አባላት ምርጫ በቤተክርስትያናችን ተከናወነ፡፡

የእለቱ የቅዳሴ አገልግሎት እንደተጠናቀቀ የተጀመረው የምርጫ ሂደት በጸሎት የተከፈተ ሲሆን ከአስመራጭ ኮሚቴው አጭር የአካሄድ ገለጻ በኋላ ማህበረ ክርስትያኑ ቤተክርስትያናችንን በትጋት ያገለግላሉ ብሎ ያመነባቸውን እጩዎች መርጧል፡፡

የምርጫው ሂደት በከፊል
የምርጫው ሂደት በከፊል

በአምላክ እርዳታ በአካሄዱ እጅግ የተዋጣለት የነበረው የምርጫ ሂደት ከጥቂት ሰአታት ቆይታ በኋላ በጸሎት የተጠናቀቀ ሲሆን በአስመራጭ ኮሚቴው፣ በተመራጭ እጩዎች እንዲሁም በምእመናኑ መካከል የታየው ክርስትያናዊ ስነ ስርአት እና መከባበር ለታዘበው እጅግ አስደሳች ነበር፡፡

ምን እንጸልይ?

 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ሚያዝያ 9 – 2008 (March 17, 2016) እሑድ በደብረ ኃይል ጎተንበርግ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ከተሰጠው ትምህርት ውስጥ የተወሰደ፡፡

ርእስ – ምን እንጸልይ?

ውዳሴ ማርያም

 1. የዘወትር ጸሎት
 2. የዕለት ውዳሴ ማርያም
 3. አንቀጸ ብርሃን
 4. ይዌድስዋ መላእክት
 5. አባታችን ሆይ
 1. መዝሙረ ዳዊት

መዝሙረ ዳዊት ሁሉም ጸሎት ነው፡፡ የየቀኑን መዝሙር ለመጸለይ አከፋፈሉ የሚከተለውን ይመስላል፡፡

 • ሰኞ፡- መዝ. 1 – 30
 • ማክሰኞ ፡- መዝ. 31 – 60
 • ረቡዕ፡- መዝ.   61 – 80
 • ሐሙስ፡- መዝ.  81 – 110
 • ዓርብ፡- መዝ.   111 – 130
 • ቅዳሜ፡- መዝ.  131 – 150፤ መኃል. መኃ. ዘሰሎሞን
 • እሑድ፡- ጸሎተ ነቢያት

የየቀኑን ማድረስ ካልተቻለ

በየቀኑ አንድ፤ አንድ ንጉሥ (አሥር፤ አሥር መዝሙራትን) መጸለይ

 ልዩ ጸሎት  መዝ. 118(119) ፡ 1 – 176

አሥር አሥር መዝሙራትን ለማድረስ ካልተቻለ ጊዜ የሌለው ሰው ቢያንስ የሚከተሉትን መርጦ ቢጸልይ መልካም ነው::

መዝሙረ ዳዊት 6

መዝሙረ ዳዊት 12 (13)

መዝሙረ ዳዊት 19 (20)

መዝሙረ ዳዊት 22 (23)

መዝሙረ ዳዊት 24 (25)

መዝሙረ ዳዊት 26 (27)

መዝሙረ ዳዊት 37 (38)

መዝሙረ ዳዊት 50 (51)

መዝሙረ ዳዊት 69 (70)

መዝሙረ ዳዊት 85 (86)

መዝሙረ ዳዊት 90 (91)

መዝሙረ ዳዊት 120 (121)

መዝሙረ ዳዊት 135 (136)

መዝሙረ ዳዊት 140 (141)

መዝሙረ ዳዊት 144 (145)

 1. ጸሎተ ነቢያት

የእስራኤላውያን ምስጋና (ዘጸአት 15 ፤ 1 – 19)

የሙሴ ጸሎት (ዘዳግም 32 ፤ 1 – 43)

የሳሙኤል እናት የሐና ጸሎት (1 ሳሙ. ፤ 1 – 10)

የምናሴ ጸሎት (2 ዜና መዋ. 33 : 12 – 13)

የነቢዩ የኢሳይያስ ጸሎት (ኢሳ. 26 ፤ 1 – 21)

የንጉሡ የሕዝቅያስ ጸሎት (ኢሳ. 38 ፤ 10 – 20)

የነቢዩ የዳንኤል ጸሎት (ዳን. 9 ፤ 4 – 19)

የነቢዩ የዮናስ ጸሎት (ዮና. 2 ፤ 3 – 11)

ጸሎተ ሠለስቱ ደቂቅ (የጸሎት መጻሕፍት)

የሦስቱ ልጆች መዝሙር (የጸሎት መጻሕፍት)

የነቢዩ የዕንባቆም ጸሎት (ዕንባ. 3 ፤ 1 – 19)

የድንግል ማርያም ጸሎት (ሉቃ. 1 ፤ 46 – 55)

የካህኑ የዘካርያስ ጸሎት (ሉቃ. 1 ፤ 68 – 79)

የነቢዩ የስምዖን ጸሎት (ሉቃ. 2 ፤ 29 – 32)

ከነዚህ ውስጥ የምናሴ ጸሎት፣ ጸሎተ ሠለስቱ ደቂቅ፣ የሦስቱ ልጆች መዝሙር የሚሉት የጸሎት መጻሕፍት ውስጥ እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኙም፡፡

 1. ውዳሴ አምላክ
 • የቀን፤ የቀን ጸሎት ያለው ሲሆን የሚከተሉት የዳዊት መዝሙራት በየቀናቱ መጨረሻ ላይ ይገኛሉ፡፡
 • መዝሙረ ዳዊት 6
 • መዝሙረ ዳዊት 24 (25)
 • መዝሙረ ዳዊት 37 (38)
 • መዝሙረ ዳዊት 50 (51)
 • መዝሙረ ዳዊት 69 (70)
 • መዝሙረ ዳዊት 85 (86)፤
 • መዝሙረ ዳዊት 120 (121)
 1.   ወንጌል ዘዮሐንስ

ወንጌለ ዮሐንስ ሃያ አንድ ምዕራፎች አሉት፡፡ በሳምንት ለመጨረስ ሦስት፤ ሦስት ምዕራፍ በሦስት ቀን ለመጨረስ ሰባት፤ ሰባት ምዕራፍ ካልተቻለም በየቀኑ አንድ፤ አንድ ምዕራፍ ብቻ ይጸለያል፡፡

6. ሌሎች ጸሎታት

 • አርጋኖን፡- የቀን፤ የቀን ጸሎት ያለው ሲሆን የእመቤታችንን ምስጋናና ልመና የያዘ ጸሎት ነው፡፡
 • ልክአ መልክእ፡- መልክአ መድኃኔ ዓለም፤ መልክአ ሥላሴ፤ መልክአ ኢየሱስ፤ መልክአ ማርያም፣ የቅዱሳን መልክእ . . .
 • በመጨረሻም አርባ አንድ ኪርያላይሶንና እግዚኦታ (ከስግደት ጋር)

 

እንደ ዓይነተኛ ምሳሌ አንድ መካከለኛ ደረጃ ላይ ያለ ምእመን የሚያደርሰው ጸሎት

 1. ጧት
  1. የዘወትር ጸሎት
  2. የዕለት ውዳሴ ማርያም
  3. ይዌድስዋ መላእክት
  4. ውዳሴ አምላክ የዕለቱን
  5. አርባ አንድ ኪርያላይሶንና እግዚኦታ (ከስግደት ጋር)
  6. አባታችን ሆይ
 2. ማታ
  1. አንቀጸ ብርሃን
  2. የዮሐንስ ወንጌል (አንድ ወይም ሥስት ምዕራፍ)
  3. መዝሙረ ዳዊት (አንድ ወይም 3 መዝሙራት)
  4. አባታችን ሆይ

አንዱ የጸሎት ዓይነት ሲያልቅ ወደሌላው ከመሸጋገር በፊት በአባታችን ሆይ ይዘጋል፡፡

እንደ ጊዜያችን ሁኔታ የጧትና የማታውን ጸሎት ስግደቱንም ጭምር ማሸጋሸግ ይቻላል፡፡

 ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል አሜን

ማስታወቂያ – የልደት በዓል

ዘንድሮ የጌታችንና የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት ታኅሣሥ 28 ቀን 2008 (Jan. 7, 2016) ይከበራል፡፡

ስለሆነም ቤርሾዳለን 44 በሚገኘው የደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ከላይ በተገለጸው ቀን ረቡዕ ለሐሙስ ሌሊት ከምሽቱ 21፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ 00፡30 ድረስ ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ፕሮግራሞች የሚካሄድ ሲሆን ጸሎተ ቅዳሴውም ከሌሊቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ እስከ 3፡00 ሰዓት ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ይከናወናል፡፡

እርስዎም 2008 ዓመታት ወደ ኋላ በሃሳብ ተመልሰው በቤተልሔም ከተማ በከብቶች ግርግም ክርስቶስ የተወለደበትን ሌሊት እያስታወሱ ለአምላክዎ ምስጋና በማቅረብ ከክርስቲያን ወገኖችዎ ጋራ በጣም ጣፋጭ የበረከት ሌሊት ለማሳለፍ በምሽት ወደ ቤተክርስቲያናችን ብቅ ይሉ ዘንድ ተጋብዘዋል፡፡

ሰላመ እግዚአብሔር አይለየን፡፡

የደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤልና ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን፡፡

ዓመታዊ የታኅሣሥ ገብርኤል በዓል

ዓመታዊው የታኅሣሥ ገብርኤል በዓል ታኅሥሥ 17- 2008 (December 27 – 2015) እሑድ ቀን የሚከበር ሲሆን በዓሉንም በደማቅ ሁኔታ ለማክበር በደብሩ ሰበካ ጉባኤ የተጋበዙ ሁለት አባቶች ከእንግሊዝና ከጀርመን ይመጣሉ፡፡ ስለሆነም በዕለቱ ከሚኖረው ሰፋ ያለ መርሐ ግብር በተጨማሪ የበዓሉ ዋዜማ ቅዳሜ ማታ ከ16፡00 ጀምሮ የዋዜማ ቁመትና የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብር ይደረጋል፡፡ ስለዚህ የታላቁ መልአክ የቅዱስ ገብርኤል ወዳጆች የሆናችሁ ሁሉ በዕለቱም ሆነ በዋዜማው ቀን “Bergsjodalen 44″ በሚገኘው የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በመገኘት ከበዓሉ በረከት ትሳተፉ ዘንድ ቤተ ክርስቲያናችን ጥሪዋን ታቀርባለች፡፡

ሰላመ እግዚአብሄር ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡ አሜን

መጽናናት-ክፍል ፩

መቼም ሰው ማኅበራዊ እንሰሳ ነው ሲባል ሰምታቹህ ይሆናል። ማኅበራዊ የሚለው ጥሩ ገላጭ ቃል ሚዛኑን ያስተካክለዋል እንጂ ሰውን አንሰሳ ማለት የሚከብድ ይመስላል። በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ሰው ለሰው ምን ያህል ጉልህ ተጽእኖ እንዳለው የተሰወረ አይደለም። እስኪ በዚህ መነሻነት ብዙ ኃሳቦችን መዳሰስ ቢቻልም ስለ መጽናናት ብናወጋስ? ምክንያቱም መንፈሳዊ መጽናናት፣ ከያለንበት ማንኛውም አመልካከት ከፍ ወዳለ መልካም ደረጃ ይመራናልና። ይህ ርዕስ ሰፊ ቢሆንም በየጊዜው በትንሽ በትንሹ እናዳብረዋለን።

በመንፈሳዊ ዕይታ፣ መጽናናት በአንድም ይሁን በሌላ ከራሳችን ውጪ ከተጨማሪ አካል ጋራ ይገናኛል። እንዲሁም መጽናናት እንደተመልካቹ የአመለካከት ሁኔታ ይወሰናል። ለመነሻነት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው ፪ኛ መልእክቱ ምዕራፍ ፯ ቁጥር ፮ (7፥6) ላይ ስንመለከት እንዲህ ይላል፡ ነገር ግን ኀዘንተኞችን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናን”። እዚህ ላይ የምንመለከተው ፣ ዋናው አጽናኝ አምላካችን እግዚአብሔር ሲሆን ፣ ቲቶ ደግሞ የአምላክ መልካምነቱ መገለጫ ሆነ ማለት ነው።

አምላክ በሰዎች በመገለጥ መልካሙን ሲተገብር አስቀድመን አምላክን በማመስገን ቀጥለን ደግሞ የመልካም ምግባር ተመራጭ እና ተግባሪ የሆነውን ሰው እናመሰግንበታለን፥ እንመርቃለን፥ መልካም እንመኝለታለን። በተጨማሪም በሐሳባችን፥ ትካዜያችን፥ ደስታችን፥ ትሕትናችን፥ ምኞታችን በአጠቃላይ አመለካከታችን በሚታየው ነገር ላይ ብቻ ሳይሆን በማይታየው የመልካም ነገሮች ምንጭ ወደ ሆነው አምላክ ዞሮ የሚገጥም ከሆነ፤ በኃዘንም ውስጥ ከአምላክ ጋር ፈገግታ፣ በደስታም ውስጥ በተረጋጋ የሐሴት ፈገግታ በመሆን አምልኮታችንን እናጠናክርበታለን።

መንፈስ ቅዱስ የመራው ጳውሎስ፣ በአለማዊ ዓይኑ የቲቶን መምጣት ተመልክቶ ሳያበቃ፣ በመንፈሳዊው ዓይኑ የእግዚአብሔርን ስራ ተመለከተ። እኛም በምድራዊ ዓይናችን ላይ ብቻ ሳንገደብ፣ ከምናየው ጀርባ ሊኖሩ በሚችሉ መልካም አቅጣጫዎች ብናተኩር ገንቢ ነው። ለማዘንማ እጅግ ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ፣ ጳውሎስ ያልጎበኙትን በማሰብ መማረር በቻለ። ግን ለምን? የሚያመሰግንበት ጥቂት ምክንያት እያለው ስለምን በሚከፋበት ሰፊ ጉድለት ላይ ይመሰጥ? እኛስ በሕይወታችን ውስጥ በሰዎች በኩል የተካፈልናቸው መረዳቶች፥ መታገዞች፥ መረጋጋቶች፥ ኃሳብ መካፈሎች፥ አቅጣጫ ጥቆማዎች፥ ፈገግታዎች፥ ድጋፎች እና የመሳሰሉትን በልባችን በማቆየት የሚያጋጥሙንን መልካም ያልሆኑ ክንዋኔዎች ብንወጣበትስ? መጎዳታችን ወደ ተሻለ አቅጣጫ እንድናቀና የመንቂያና መትጊያ ተነሳሽነት መጨመሪያ እንጂ፤ መማረር ፥ ብስጨት፥ ሀዘን፥ ወቀሳ የመሳሰሉትን፣ የበለጠ መከፋትን የሚያላብሱ እንዳይሆኑብን፣ ከዚህ የጳውሎስ ቃል እንገነዘባለን።

ጽሑፉ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይቀጥላል።

ስብሐት ለእግዚአብሔር።

ምኞትና ምስጋና

እንኳን ለበዓለ መድኃኔዓለም አደረሳችሁ።

የእግዚአብሔር ትዕግስት” ከሚለው መጽሐፍ ምዕራፍ አራት ላይ የተወሰደ ጽሑፍ እናካፍላቹ።

ሙሉ እግር የሌለው አንድ ሰው እጅግ ያማረ ለምለም መስክ አይቶ ቁጭ አለና፦ “አይ ይሄ መስክ በእግር እየተራመዱ ቢያቋርጡት እንዴት መልካም ነበር?” ብሎ ተመኘ። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ሌላ እግረኛ መጣና፦ “አይ ይሄ መስክ በፈረስ እየጋለቡ ቢያቋርጡት እንዴት መልካም ነበር?” አለ። ይህን ያዳመጠው የመጀመርያው ወገን፦ “አይ አንተ እግዚአብሔር፣ ማን ነው ባለው የሚያመሰግንህ?” አለ ይባላል።

መጽሐፉን እንዲያነቡት እየጋበዝን፣ መልካሙን ሁሉ መመኘት መልካም ቢሆንም ባለን ማመስገንን ደግሞ የበለጠ መልካም ነው እንላለን። ስለዚህ መመኘት፣ የሀዘን ስሜትን እንዲፈጥርብን ሳይሆን፣ ያለንን ነገር አስተውለን፦ “መድኃኔዓለም፡ ያደረክልኝ እኮ ይበልጣል” ብለን በማመስገን አካላችንን እና መንፈሳችንን በፈገግታ ልናደምቀው ይገባል እንላለን። እስኪ ከመጽሐፍ ቅዱሳችን ተዛማች የሆነ ጥቅስ ቃል በቃል በማቅረብ እንጨርስ፦

“በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና። ማንም ሲፈተን። በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም። ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል። ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች። የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ አትሳቱ።” የያዕቆብ መልእክት ምዕራፍ ፩፥፲፪-፲፮ (1፥12-16)

ምስጋና ይሁን ለአብ፥ ለወልድ፥ ለመንፈስ ቅዱስ፥ አንድ አምላክ ዛሬም፥ ዘወትርም፥ ለዘለዓለም። አሜን።

የሃሎዊን በዓል

ከተለያዩ መንፈሳዊ ድረ ገጾች የተውጣጣ

የዘመኑ ስልጣኔ በጣም ብዙ በጐ ነገሮች እንዳሉት ሁሉ በተቃራኒውም ትውልዱ የእግዚአብሔር የሆነውን ሁሉ እንዲቃውምና እንዲጠላ ከማድረግ ባሻገር በብዙ የሰይጣን ፍላጻ የተወጋ እንዲሆን አድርጎታል።

የሰይጣንን ክፋት የሚገልጠው የእግዚአብሔር መጽሐፍ ቅዱስ ተዘግቶ የሰይጣን መጽሐፍና የተለያዩ የሰማዩን መንግሥት የሚቃወሙ ጽሑፎችና ፊልሞች በፍጥነት ወደ ትወልዱ እየተሰራጩ ይገኛሉ። በዚህም በሽታ አፍሪካን እና የተለያዩ ዓለማትን ጨምሮ በተለይ በምዕራቡ ዓለም ባሉ ትልልቅ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የሚማሩ ተማሪዎች በግልጽ ተነድፈዋል። ለዚህም ማለማመጃ ካደረጋቸው በርካታ መንገዶች አንዱ  በምዕራባውያኑ ሃሎዊን ተብሎ የሚጠራው በዓል ነው።

ሃሎዊን October 31 ቀን የሚከበር በዓል ሲሆን ኖቬምበር 1 ቀን ደግሞ የሁሉም ቅዱሳን ቀን ወይም በእንግሊዝኛው “All Hallow’s Day” ተብሎ በዘመናት ሰማዕታት የሆኑ ቅዱሳን ይከበሩ ነበር፡፡ ከዚህ ቀን በፊት ያለው የዋዜማ ቀን – October 31 የቅዱሳን ዋዜማ ቀን ወይም በእንግሊዝኛው “All Hallow’s Eve” እየተባለ ሲጠራ ቆይቶ ሰብሰብ፣ አጠር ተደረገና “Hallow-e’en,” ከዚያም በመጨረሻ “Halloween” ተባለ፡፡

Continue reading የሃሎዊን በዓል

ሃሎዊንና ብዥታው

በዚህ ጉዳይ ጠለቅ ያለ ጽሑፍ እስኪቀናበር ድረስ ጊዜው ሳያልፍብን በጥቂቱ መሰረታዊ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው።

ከ2000 ዓመታት በፊት አውሮፓ ውስጥ በተለይ በሴልቲክ ግዛት ይባል በነበረው ክልል ውስጥ የነበሩ ማህበረሰቦች November 1 በተለይ በዋዜማው “ክፉ መንፈስ በአከባቢያችን በመገኘት ጥፋት ያደርሳሉና ሰው መሆናችን እንዳያውቁብን ራሳችንን በተለያዩ ማስመሰያዎች እነሱን መስለን ከታየን አይነኩንም አልፈውንም ይሔዳሉ” በሚል እምነት የነበረ አካሄድ ነበር።

ከጊዜያት በኃላ ይህን አካሄድ ለመሻርና ለማስረሳት ሲባል በተመሳሳይ ቀን የቅዱሳን ቀን የሚባል በዓል ተመሰረተ። ዋዜማውም “የቅዱሳን ቀን ዋዜማ” ወይም Halloween እየተባለ በመልካም ዓላማ ላይ ተሰይሞ የተሻለ እንቅስቃሴ ነበር። ከዚህ በጎ ስሙን ብቻ በመጠቀም በድርጊት ግን የጥንቱን ክፉ መስሎ መታየትን ያገዘፈ አካሄድ በአሁኑ ወቅት እየተንሰራፋ ይገኛል።

ለማንኛውም አላስፈላጊ ክርክርን አስወግዶ የሁኔታዎቹን አመጣጥ ግን አጥርቶና ተረድቶ በሰላምና በፍቅር መንቀሳቀስ ለሁሉም ይበጃል።

የእግዚአብሔር ሰላም ከሁላችን ጋር ይሁን። አሜን።

የድረ ገጽ እንከን

ድረ ገጻችን ሊገጥመው የሚችለውን የመበላሸት ችግር ለመቋቋም የሚያስችሉ አሰራሮችን በመተግበር በአዲስ ሁኔታ ተደራጅቶ አገልግሎቱን ቀጠለ።

ለተወሰኑ ቀናት ይታይ የነበረው የመዘግየትና ከሌሎች ድረ ገጾች ጋር የመፋለስ ችግሮች ተቀርፈዋል።

እግዚአብሔር ይመስገን። አሜን።