Category Archives: ጽሑፎች

መንፈሳዊ ጉባኤ ጥሪ በጎተንበርግ

በኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጎተንበርግ
ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤልና ቅዱስ ጊዬርጊስ ቤተ ክርስቲያን
፳፪ (22) ኛውን የአውሮፓ ታላቅ መንፈሳዊ ጉባኤ
ተሳታፊ እንድትሆኑ በእግዚአብሔር ስም ተጋብዘዋል።

በኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጎተንበርግ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤልና ቅዱስ ጊዬርጊስ ቤተ ክርስቲያን ፳፪ (22) ኛውን የአውሮፓ ታላቅ መንፈሳዊ ጉባኤ ተሳታፊ እንድትሆኑ በእግዚአብሔር ስም ተጋብዘዋል።

ቤተክርስቲያናችን የመንፈሳዊ ዜማ ኮንፈረንስ ላይ ተሳተፈች …

የቤተክርስቲያናችን ሰንበት ትምህርት ቤት በጎተንበርግ ከተማ በተደረገ የመንፈሳዊ ዜማ ኮንፈረንስ ላይ ከአባቶች እንዲሁም ከመመናኑ ጋር በመሆን  የደመቀ ተሳትፎ አድርጓል

በእለቱም የተለያዩ ወቅቱን የሚያወሱ ያሬዳዊ ዜማዎች የቀረቡ ሲሆን ለተገኙትም ታዳሚዎች ስለዜማዎቹ ይዘት እና ምንጭ መጠነኛ ገለጻ ተደርጓል

20160910_095029

 

አመታዊው የመስቀል ደመራ በአል በደማቅ ሁኔታ ተከበረ …

እንደቀደሙት አመታት ሁሉ የዘንድሮውም የመስቀል ደመራ ክብረ በአል በደመቀ ሁኔታ ተከብሯል

በእለቱ ከበድ ያለ ዝናብ ቢጥልም  የተገኘው በዛ ያለ ምእመን በአሉን በደማቅ ሁኔታ አክብሮት አምሽቷል

ማስታወቂያ

ባለፈው እሑድ መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ ም (Oktober 2 – 2016) በደብረ ዘይት (ቢሾፍቱ) በሚከበረው ባህላዊ የእሬቻ በዓል ላይ ባሳዛኝና ባሰቃቂ ሁኔታ ሕይወታቸው ላጡ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ነገ እሑድ መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ ም (Oktober 9 – 2016) Bergsjödalen 44 በሚገኘው የደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤልና ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የዕለቱ ሥርዓተ ቅዳሴ ከተጠናቀቀ በኋላ ጸሎተ ምሕላና ጸሎተ ፍትሐት ይደረጋል፡፡
ስለዚህ ይህ ጥሪ የደረሳችሁ ሕዝበ ክርስቲያን በሙሉ ከላይ በተገለፀው ቦታ በሰዓቱ በመገኝት በሚካሔደው ጸሎተ ምሕላና ጸሎተ ፍትሐት ላይ ተካፋይ ትሆኑ ዘንድ ላልሰሙትም እንዲያሰሙ በእግዚአብሔር ስም ጥሪያችንን እናቀርባለል።

የጎተንበርግ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤልና ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን፡፡

የእግዚአብሔር ሰላም ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡

መንፈሳዊ ደስታ

መንፈሳዊ ደስታ

መንፈሳዊ ደስታ ውጤቱ እጽፍ ድርብ የሆነ ዘለአለማዊ ደስታ ነው:: ሐዋርያት ጌታን ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው እርሱም ሰላም ለእናንተ ይሁን . . እንደገና አያችኋለሁ ልባችሁም ደስ ይለዋል ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም” በማለት ማንም የማይቀማቸው ደስታ መሆኑንና ዘለዓለማዊ መሆኑን ነግሯቸዋል (ዩሐ.16 ፥ 22 ፣ ዩሐ. 20 ፥ 20)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ሁል ጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ ደግሜ እላለሁ ደስ ይበላችሁ” በማለት ለሰው ልጆች የሚጠቅመውን ምክር ሰጥቷል (ፊል.4፥4):: እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ደግሞ የደስታን ታላቅነትና ዘለአለማዊነት እንዲህ ስትል ትገልጻለች ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች” (ሉቃ. 1፥ 47):: እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ደስ የሚያሰኝ ድምፅና ምስጋና ትሰማ ነበር:: ጌታን በፀነሠች ጊዜ ቅዱሳን መላእክት ማኅፀንዋን ዓለም አድርገው ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር እያሉ በማኅፀንዋ ሲያመሠግኑ ትሰማ ነበርና (አረጋዊ መንፈሳዊ ገጽ 25)

ሌላው የወንጌል አስደሳችነት በዕርቅና በንሰሐ ኃጢአትን በማስወገድ የሚገኝ ደስታ ነው:: ሰው ሁሉ ከኃጢአትና ከልዩ ልዩ መጥፎ ልማዶች በቃለ ወንጌል ነፃ ሲወጣ ፣ በንሰሐ ኃጢአትን ድል ሲነሳ፣ ይቅርታን ሲያገኝ እጅግ ደስ ይለዋል:: ይህ ደስታ የጠፋው ልጅ ወደ አባት ቤት በመመለሱ የተደሰተው ደስታ ነው (ሉቃ.15 ፥ 24)፡፡ ነቢዩ ዳዊትም ምን እንዳለ እንመልከት በሂሶጵ እርጨኝ እነፃለሁ እጠበኝ ከበረዶም ይልቅ ንፁህ እሆናለሁ ሐሴትንና ደስታን አሰማኝ የጻድቃንም አጥንቶችም ደስ ይበላቸው” (መዝ.50፥8):: ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ” በማለት በተደጋጋሚ ተናግሯል (መዝ. 121፥1):: ይህ ደስታ ሰው ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ሲገናኝ ዘላለማዊ የሆነ ደስታ እንደሚያገኝ የሚገልጽ ነው። መጥምቁ ዩሐንስ “ሙሽራ ያለችው ሙሽራ ነው ቆሞ የሚሰማው የሙሽራው ሚዜ ግን በሙሽራው ቃል እጅግ ደስ ይለዋልየእኔ ደስታ አሁን ተፈፀመች” ብሏል (ዩሐ.3 ፥ 29)፡፡ ይህ ደስታ ከራስ ምኞት ነፃ የሆነ መንፈሳዊ ደስታ ነው። በወንጌል ትምህርት ሕዝቡን ከእግዚአብሔር ጋር አገናኝቷል። “በልቅሶ የሚዘሩ በደስታ ያጭዳሉ” (መዝ.125 ፥ 5) በእግዚአብሔር ፍቃድ የሚሠሩ ከፍሬው የተነሳ ደስተኞች ናቸው። ቅዱስ ጳዉሎስ “ኃዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል” (2 ቆሮ. 6 ፥ 10) ካለ በኋላ “አሁን ከመከራዬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል” ብሎ እንደተናገረ። ከእግዚአብሔር ጋር በመሆን የሚዘራና የሚያጭድ አብረው ደስ ይላቸዋል (ዩሐ.4፥36)። ቅዱስ ወንጌል ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ” ይላልና (ሮሜ. 12፥15)። እኛ በክርስቶስ አንድ አካል ነን። አንድ ሰው በቃለ ወንጌል ቢደሰት ሌሎችም ሰዎች ከእርሱ ጋር እና በእርሱ ይደሰታሉ። በሰዎች ደስታ መካፈል መልካም ምግባር ነውና (ሉቃ.15 ፥ 10)፡፡ የኤልሳቤጥ ዘመዶችና ጎረቤቶች ለቅድስት ኤልሳቤጥ ጌታ ምሕረቱን እንዳደረገላት ሰምተው ከኤልሳቤጥ ጋር ደስ አላቸው (ሉቃ.1 ፥ 57)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በቃለ ወንጌል የተደሰቱትን ምእመናንን እንዲህ ሲል አመስግኗል “እነሆ እናንም እኛንና ጌታን መሰላችሁ በብዙ መከራ ከመንፈስ ቅዱስ ደስታ ጋር ተቀብላችኋል ለሌሎች ሰዎችም ሁሉ ምሳሌ ሆናችኋል የጌታችንን ቃል ከእናንተ ሰምተው ተምረዋልና ደግሞም በእግዚአሔር ማመናችሁ በየሀገሩ ተሰምቷል” (1 ተስ 1፥6–10)፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም አሁንም በጌትነቱ በተገለጠ ጊዜ ደግሞ ድስ ብሏችሁ ሐሴት እንድታደርጉ ክርስቶስን በመከራ ትመስሉት ዘንድ ደስ ይበላችሁ፤ ስለ ክርስቶስ ስም ብትነቀፉ ብፁዓን ናችሁ” በማለት የወንጌል አስደሳችነት ከመከራ ሁሉ እንደሚያወጣ አስገንዝቧል (1 ጴጥ. 4 ፥ 13፤ ሐዋ. 5 ፥ 41)፡፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስ ከሆነ ደስታ ነው እንጂ መብልና መጠጥ አይደለምና ፤ በቃለ ወንጌል ለክርስቶስ የሚገዛ ግን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና በሰውም ዘንድ የተመረጠ ነው፡፡

አህዛብም የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው ደስ አላቸው የእግዚአብሔርም ቃል በየሀገሩ ሁሉ ተዳረሰ መንፈስ ቅዱስም በደቀ መዛሙርቱ ላይ ሞላ ደስም አላቸው (ሮሜ 14 ፥17 ፣ ሐዋ. 13 ፥ 52)፡፡ ጌታም “በፍቅሬ ኑሩ ደስታዬ በእናንተ ይኖር ዘንድ ደስታችሁም ፍፁም ይሆን ዘንድ” እንዳለው ፤ ደስታችን ፍፁም መሆኑን አረጋግጠናል፡፡ ነቢዩ ዳዊት “ነፍሴ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይላታል በማዳኑም ሐሴት ታደርጋለች” (መዝ. 33 ፥ 9)። የሰው ልጆችም በክንፎችህ ጥላ ይታመናሉ ከቤትህ ጠል ይረካሉ ከደስታህም ፈሳሽ ታጠጣቸዋለህ የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነውና” (መዝ. 34 ፥ 8) የዋሆች ምድርን ይወርሳሉ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል ርስታቸውም ለዘለዓለም ነው” ብሏል (መዝ. 35 ፥ 11)። በመቀጠልም “አቤቱ የፊትህ ብርሃን በላያችን ታወቀ በልባችን ደስታን ጨመርህ ፤ ከስንዴ ፍሬና ከወይን ዘይትም ይልቅ በዛ በአንተ የሚታመኑት ሁሉ ለዘለዓለሙ ደስ ይላቸዋል” (መዝ. 4 ፥ 7 ፣ መዝ. 5 ፥ 11)፡፡ በማለት ቅዱስ መጽሐፋችን መንፈሳዊ አስደሳችነትን በተደጋጋሚ ገልጿል፡፡ መልአኩም እንዲህ አለ እነሆ ለእናንተ ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን ታላቅ የምስራች እነግራችኋለሁ አትፍሩ” (ሉቃ. 2 ፥ 10)፡፡ ሕዝቡም ሁሉ ቃለ ወንጌልን ሲሰሙ ፈጽሞ ደስ እንዳላቸው ቅዱስ ማርቆስ እንዲህ ሲል ጽፎልናል ሕዝቡም ደስ ብሎአቸው ያዳምጡት ነበር” (ማር. 12 ፥ 37)። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የወንጌልን አስደሳችነት ምድራዊና ጊዜያዊ ብቻ አለመሆኑን ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ሲል አስረድቶአቸዋል ነገር ግን አጋንንት (መናፍስት) ስለተገዙላችሁ ደስ አይበላችሁ ግን ስማችሁ በመንግሥተ ሰማያት ስለተጻፍ ደስ ይበላችሁ” (ሉቃ. 10 ፥ 20)፡፡ ሕገ ወንጌልን ጠብቀውና በታማኝነት የሚኖሩ ሁሉ ወደ ዘለዓለም ደስታ እንደሚገቡም እንዲህ ሲል አስተምሯል ጌታውም መልካም አንተ የታመንህ በጎ አገልጋይ ፤ በጥቂቱ የታመንህ ስለሆንክ በብዙ እሾምሃለሁ ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው” (ማቴ. 25 ፥ 21)፡፡

ወስበሐት ለእግዚአብሔር፤ ወለወላዲቱ ድንግል፤ ወለመስቀሉ ክቡር

 

መጽናናት-ክፍል ፩

መቼም ሰው ማኅበራዊ እንሰሳ ነው ሲባል ሰምታቹህ ይሆናል። ማኅበራዊ የሚለው ጥሩ ገላጭ ቃል ሚዛኑን ያስተካክለዋል እንጂ ሰውን አንሰሳ ማለት የሚከብድ ይመስላል። በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ሰው ለሰው ምን ያህል ጉልህ ተጽእኖ እንዳለው የተሰወረ አይደለም። እስኪ በዚህ መነሻነት ብዙ ኃሳቦችን መዳሰስ ቢቻልም ስለ መጽናናት ብናወጋስ? ምክንያቱም መንፈሳዊ መጽናናት፣ ከያለንበት ማንኛውም አመልካከት ከፍ ወዳለ መልካም ደረጃ ይመራናልና። ይህ ርዕስ ሰፊ ቢሆንም በየጊዜው በትንሽ በትንሹ እናዳብረዋለን።

በመንፈሳዊ ዕይታ፣ መጽናናት በአንድም ይሁን በሌላ ከራሳችን ውጪ ከተጨማሪ አካል ጋራ ይገናኛል። እንዲሁም መጽናናት እንደተመልካቹ የአመለካከት ሁኔታ ይወሰናል። ለመነሻነት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው ፪ኛ መልእክቱ ምዕራፍ ፯ ቁጥር ፮ (7፥6) ላይ ስንመለከት እንዲህ ይላል፡ ነገር ግን ኀዘንተኞችን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናን”። እዚህ ላይ የምንመለከተው ፣ ዋናው አጽናኝ አምላካችን እግዚአብሔር ሲሆን ፣ ቲቶ ደግሞ የአምላክ መልካምነቱ መገለጫ ሆነ ማለት ነው።

አምላክ በሰዎች በመገለጥ መልካሙን ሲተገብር አስቀድመን አምላክን በማመስገን ቀጥለን ደግሞ የመልካም ምግባር ተመራጭ እና ተግባሪ የሆነውን ሰው እናመሰግንበታለን፥ እንመርቃለን፥ መልካም እንመኝለታለን። በተጨማሪም በሐሳባችን፥ ትካዜያችን፥ ደስታችን፥ ትሕትናችን፥ ምኞታችን በአጠቃላይ አመለካከታችን በሚታየው ነገር ላይ ብቻ ሳይሆን በማይታየው የመልካም ነገሮች ምንጭ ወደ ሆነው አምላክ ዞሮ የሚገጥም ከሆነ፤ በኃዘንም ውስጥ ከአምላክ ጋር ፈገግታ፣ በደስታም ውስጥ በተረጋጋ የሐሴት ፈገግታ በመሆን አምልኮታችንን እናጠናክርበታለን።

መንፈስ ቅዱስ የመራው ጳውሎስ፣ በአለማዊ ዓይኑ የቲቶን መምጣት ተመልክቶ ሳያበቃ፣ በመንፈሳዊው ዓይኑ የእግዚአብሔርን ስራ ተመለከተ። እኛም በምድራዊ ዓይናችን ላይ ብቻ ሳንገደብ፣ ከምናየው ጀርባ ሊኖሩ በሚችሉ መልካም አቅጣጫዎች ብናተኩር ገንቢ ነው። ለማዘንማ እጅግ ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ፣ ጳውሎስ ያልጎበኙትን በማሰብ መማረር በቻለ። ግን ለምን? የሚያመሰግንበት ጥቂት ምክንያት እያለው ስለምን በሚከፋበት ሰፊ ጉድለት ላይ ይመሰጥ? እኛስ በሕይወታችን ውስጥ በሰዎች በኩል የተካፈልናቸው መረዳቶች፥ መታገዞች፥ መረጋጋቶች፥ ኃሳብ መካፈሎች፥ አቅጣጫ ጥቆማዎች፥ ፈገግታዎች፥ ድጋፎች እና የመሳሰሉትን በልባችን በማቆየት የሚያጋጥሙንን መልካም ያልሆኑ ክንዋኔዎች ብንወጣበትስ? መጎዳታችን ወደ ተሻለ አቅጣጫ እንድናቀና የመንቂያና መትጊያ ተነሳሽነት መጨመሪያ እንጂ፤ መማረር ፥ ብስጨት፥ ሀዘን፥ ወቀሳ የመሳሰሉትን፣ የበለጠ መከፋትን የሚያላብሱ እንዳይሆኑብን፣ ከዚህ የጳውሎስ ቃል እንገነዘባለን።

ጽሑፉ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይቀጥላል።

ስብሐት ለእግዚአብሔር።

ምኞትና ምስጋና

እንኳን ለበዓለ መድኃኔዓለም አደረሳችሁ።

የእግዚአብሔር ትዕግስት” ከሚለው መጽሐፍ ምዕራፍ አራት ላይ የተወሰደ ጽሑፍ እናካፍላቹ።

ሙሉ እግር የሌለው አንድ ሰው እጅግ ያማረ ለምለም መስክ አይቶ ቁጭ አለና፦ “አይ ይሄ መስክ በእግር እየተራመዱ ቢያቋርጡት እንዴት መልካም ነበር?” ብሎ ተመኘ። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ሌላ እግረኛ መጣና፦ “አይ ይሄ መስክ በፈረስ እየጋለቡ ቢያቋርጡት እንዴት መልካም ነበር?” አለ። ይህን ያዳመጠው የመጀመርያው ወገን፦ “አይ አንተ እግዚአብሔር፣ ማን ነው ባለው የሚያመሰግንህ?” አለ ይባላል።

መጽሐፉን እንዲያነቡት እየጋበዝን፣ መልካሙን ሁሉ መመኘት መልካም ቢሆንም ባለን ማመስገንን ደግሞ የበለጠ መልካም ነው እንላለን። ስለዚህ መመኘት፣ የሀዘን ስሜትን እንዲፈጥርብን ሳይሆን፣ ያለንን ነገር አስተውለን፦ “መድኃኔዓለም፡ ያደረክልኝ እኮ ይበልጣል” ብለን በማመስገን አካላችንን እና መንፈሳችንን በፈገግታ ልናደምቀው ይገባል እንላለን። እስኪ ከመጽሐፍ ቅዱሳችን ተዛማች የሆነ ጥቅስ ቃል በቃል በማቅረብ እንጨርስ፦

“በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና። ማንም ሲፈተን። በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም። ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል። ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች። የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ አትሳቱ።” የያዕቆብ መልእክት ምዕራፍ ፩፥፲፪-፲፮ (1፥12-16)

ምስጋና ይሁን ለአብ፥ ለወልድ፥ ለመንፈስ ቅዱስ፥ አንድ አምላክ ዛሬም፥ ዘወትርም፥ ለዘለዓለም። አሜን።

የሃሎዊን በዓል

ከተለያዩ መንፈሳዊ ድረ ገጾች የተውጣጣ

የዘመኑ ስልጣኔ በጣም ብዙ በጐ ነገሮች እንዳሉት ሁሉ በተቃራኒውም ትውልዱ የእግዚአብሔር የሆነውን ሁሉ እንዲቃውምና እንዲጠላ ከማድረግ ባሻገር በብዙ የሰይጣን ፍላጻ የተወጋ እንዲሆን አድርጎታል።

የሰይጣንን ክፋት የሚገልጠው የእግዚአብሔር መጽሐፍ ቅዱስ ተዘግቶ የሰይጣን መጽሐፍና የተለያዩ የሰማዩን መንግሥት የሚቃወሙ ጽሑፎችና ፊልሞች በፍጥነት ወደ ትወልዱ እየተሰራጩ ይገኛሉ። በዚህም በሽታ አፍሪካን እና የተለያዩ ዓለማትን ጨምሮ በተለይ በምዕራቡ ዓለም ባሉ ትልልቅ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የሚማሩ ተማሪዎች በግልጽ ተነድፈዋል። ለዚህም ማለማመጃ ካደረጋቸው በርካታ መንገዶች አንዱ  በምዕራባውያኑ ሃሎዊን ተብሎ የሚጠራው በዓል ነው።

ሃሎዊን October 31 ቀን የሚከበር በዓል ሲሆን ኖቬምበር 1 ቀን ደግሞ የሁሉም ቅዱሳን ቀን ወይም በእንግሊዝኛው “All Hallow’s Day” ተብሎ በዘመናት ሰማዕታት የሆኑ ቅዱሳን ይከበሩ ነበር፡፡ ከዚህ ቀን በፊት ያለው የዋዜማ ቀን – October 31 የቅዱሳን ዋዜማ ቀን ወይም በእንግሊዝኛው “All Hallow’s Eve” እየተባለ ሲጠራ ቆይቶ ሰብሰብ፣ አጠር ተደረገና “Hallow-e’en,” ከዚያም በመጨረሻ “Halloween” ተባለ፡፡

Continue reading የሃሎዊን በዓል

ሃሎዊንና ብዥታው

በዚህ ጉዳይ ጠለቅ ያለ ጽሑፍ እስኪቀናበር ድረስ ጊዜው ሳያልፍብን በጥቂቱ መሰረታዊ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው።

ከ2000 ዓመታት በፊት አውሮፓ ውስጥ በተለይ በሴልቲክ ግዛት ይባል በነበረው ክልል ውስጥ የነበሩ ማህበረሰቦች November 1 በተለይ በዋዜማው “ክፉ መንፈስ በአከባቢያችን በመገኘት ጥፋት ያደርሳሉና ሰው መሆናችን እንዳያውቁብን ራሳችንን በተለያዩ ማስመሰያዎች እነሱን መስለን ከታየን አይነኩንም አልፈውንም ይሔዳሉ” በሚል እምነት የነበረ አካሄድ ነበር።

ከጊዜያት በኃላ ይህን አካሄድ ለመሻርና ለማስረሳት ሲባል በተመሳሳይ ቀን የቅዱሳን ቀን የሚባል በዓል ተመሰረተ። ዋዜማውም “የቅዱሳን ቀን ዋዜማ” ወይም Halloween እየተባለ በመልካም ዓላማ ላይ ተሰይሞ የተሻለ እንቅስቃሴ ነበር። ከዚህ በጎ ስሙን ብቻ በመጠቀም በድርጊት ግን የጥንቱን ክፉ መስሎ መታየትን ያገዘፈ አካሄድ በአሁኑ ወቅት እየተንሰራፋ ይገኛል።

ለማንኛውም አላስፈላጊ ክርክርን አስወግዶ የሁኔታዎቹን አመጣጥ ግን አጥርቶና ተረድቶ በሰላምና በፍቅር መንቀሳቀስ ለሁሉም ይበጃል።

የእግዚአብሔር ሰላም ከሁላችን ጋር ይሁን። አሜን።

የሚያጽናኑ ጥቅሶች

በጭንቀትና በመከራ ፥ በሐዘን ጊዜ የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላትና ጥቅሶች ካስታወሳችሁ ትጽናናላችሁ።

ሠፋ ላለ ንባብ ከመጽሐፍ ቅዱስ በተጨማሪ የቅዱስነታቸው አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊን ”መንፈሳዊ ቃላትና ጥቅማቸው” የሚለውን ያንብቡ። ይህም ንባብ በዚህ መጽሐፍ የተወሰደ ነው።

  • እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ። (ማቴዎስ 28፥20)
  • እርሱ ግን (ኢየሱስም) እኔ ነኝ፤ አትፍሩ አላቸው። (ዮሐንስ 6፥20)
  • ሙሴም ለሕዝቡ። አትፍሩ፥….. ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን እግዚአብሔርን ማዳን እዩ። እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፥ እናንተም ዝም ትላላችሁ አላቸው። (ዘጸአ 14፥13-14)

Continue reading የሚያጽናኑ ጥቅሶች