መንፈሳዊ ደስታ

መንፈሳዊ ደስታ

መንፈሳዊ ደስታ ውጤቱ እጽፍ ድርብ የሆነ ዘለአለማዊ ደስታ ነው:: ሐዋርያት ጌታን ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው እርሱም ሰላም ለእናንተ ይሁን . . እንደገና አያችኋለሁ ልባችሁም ደስ ይለዋል ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም” በማለት ማንም የማይቀማቸው ደስታ መሆኑንና ዘለዓለማዊ መሆኑን ነግሯቸዋል (ዩሐ.16 ፥ 22 ፣ ዩሐ. 20 ፥ 20)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ሁል ጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ ደግሜ እላለሁ ደስ ይበላችሁ” በማለት ለሰው ልጆች የሚጠቅመውን ምክር ሰጥቷል (ፊል.4፥4):: እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ደግሞ የደስታን ታላቅነትና ዘለአለማዊነት እንዲህ ስትል ትገልጻለች ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች” (ሉቃ. 1፥ 47):: እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ደስ የሚያሰኝ ድምፅና ምስጋና ትሰማ ነበር:: ጌታን በፀነሠች ጊዜ ቅዱሳን መላእክት ማኅፀንዋን ዓለም አድርገው ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር እያሉ በማኅፀንዋ ሲያመሠግኑ ትሰማ ነበርና (አረጋዊ መንፈሳዊ ገጽ 25)

ሌላው የወንጌል አስደሳችነት በዕርቅና በንሰሐ ኃጢአትን በማስወገድ የሚገኝ ደስታ ነው:: ሰው ሁሉ ከኃጢአትና ከልዩ ልዩ መጥፎ ልማዶች በቃለ ወንጌል ነፃ ሲወጣ ፣ በንሰሐ ኃጢአትን ድል ሲነሳ፣ ይቅርታን ሲያገኝ እጅግ ደስ ይለዋል:: ይህ ደስታ የጠፋው ልጅ ወደ አባት ቤት በመመለሱ የተደሰተው ደስታ ነው (ሉቃ.15 ፥ 24)፡፡ ነቢዩ ዳዊትም ምን እንዳለ እንመልከት በሂሶጵ እርጨኝ እነፃለሁ እጠበኝ ከበረዶም ይልቅ ንፁህ እሆናለሁ ሐሴትንና ደስታን አሰማኝ የጻድቃንም አጥንቶችም ደስ ይበላቸው” (መዝ.50፥8):: ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ” በማለት በተደጋጋሚ ተናግሯል (መዝ. 121፥1):: ይህ ደስታ ሰው ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ሲገናኝ ዘላለማዊ የሆነ ደስታ እንደሚያገኝ የሚገልጽ ነው። መጥምቁ ዩሐንስ “ሙሽራ ያለችው ሙሽራ ነው ቆሞ የሚሰማው የሙሽራው ሚዜ ግን በሙሽራው ቃል እጅግ ደስ ይለዋልየእኔ ደስታ አሁን ተፈፀመች” ብሏል (ዩሐ.3 ፥ 29)፡፡ ይህ ደስታ ከራስ ምኞት ነፃ የሆነ መንፈሳዊ ደስታ ነው። በወንጌል ትምህርት ሕዝቡን ከእግዚአብሔር ጋር አገናኝቷል። “በልቅሶ የሚዘሩ በደስታ ያጭዳሉ” (መዝ.125 ፥ 5) በእግዚአብሔር ፍቃድ የሚሠሩ ከፍሬው የተነሳ ደስተኞች ናቸው። ቅዱስ ጳዉሎስ “ኃዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል” (2 ቆሮ. 6 ፥ 10) ካለ በኋላ “አሁን ከመከራዬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል” ብሎ እንደተናገረ። ከእግዚአብሔር ጋር በመሆን የሚዘራና የሚያጭድ አብረው ደስ ይላቸዋል (ዩሐ.4፥36)። ቅዱስ ወንጌል ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ” ይላልና (ሮሜ. 12፥15)። እኛ በክርስቶስ አንድ አካል ነን። አንድ ሰው በቃለ ወንጌል ቢደሰት ሌሎችም ሰዎች ከእርሱ ጋር እና በእርሱ ይደሰታሉ። በሰዎች ደስታ መካፈል መልካም ምግባር ነውና (ሉቃ.15 ፥ 10)፡፡ የኤልሳቤጥ ዘመዶችና ጎረቤቶች ለቅድስት ኤልሳቤጥ ጌታ ምሕረቱን እንዳደረገላት ሰምተው ከኤልሳቤጥ ጋር ደስ አላቸው (ሉቃ.1 ፥ 57)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በቃለ ወንጌል የተደሰቱትን ምእመናንን እንዲህ ሲል አመስግኗል “እነሆ እናንም እኛንና ጌታን መሰላችሁ በብዙ መከራ ከመንፈስ ቅዱስ ደስታ ጋር ተቀብላችኋል ለሌሎች ሰዎችም ሁሉ ምሳሌ ሆናችኋል የጌታችንን ቃል ከእናንተ ሰምተው ተምረዋልና ደግሞም በእግዚአሔር ማመናችሁ በየሀገሩ ተሰምቷል” (1 ተስ 1፥6–10)፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም አሁንም በጌትነቱ በተገለጠ ጊዜ ደግሞ ድስ ብሏችሁ ሐሴት እንድታደርጉ ክርስቶስን በመከራ ትመስሉት ዘንድ ደስ ይበላችሁ፤ ስለ ክርስቶስ ስም ብትነቀፉ ብፁዓን ናችሁ” በማለት የወንጌል አስደሳችነት ከመከራ ሁሉ እንደሚያወጣ አስገንዝቧል (1 ጴጥ. 4 ፥ 13፤ ሐዋ. 5 ፥ 41)፡፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስ ከሆነ ደስታ ነው እንጂ መብልና መጠጥ አይደለምና ፤ በቃለ ወንጌል ለክርስቶስ የሚገዛ ግን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና በሰውም ዘንድ የተመረጠ ነው፡፡

አህዛብም የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው ደስ አላቸው የእግዚአብሔርም ቃል በየሀገሩ ሁሉ ተዳረሰ መንፈስ ቅዱስም በደቀ መዛሙርቱ ላይ ሞላ ደስም አላቸው (ሮሜ 14 ፥17 ፣ ሐዋ. 13 ፥ 52)፡፡ ጌታም “በፍቅሬ ኑሩ ደስታዬ በእናንተ ይኖር ዘንድ ደስታችሁም ፍፁም ይሆን ዘንድ” እንዳለው ፤ ደስታችን ፍፁም መሆኑን አረጋግጠናል፡፡ ነቢዩ ዳዊት “ነፍሴ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይላታል በማዳኑም ሐሴት ታደርጋለች” (መዝ. 33 ፥ 9)። የሰው ልጆችም በክንፎችህ ጥላ ይታመናሉ ከቤትህ ጠል ይረካሉ ከደስታህም ፈሳሽ ታጠጣቸዋለህ የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነውና” (መዝ. 34 ፥ 8) የዋሆች ምድርን ይወርሳሉ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል ርስታቸውም ለዘለዓለም ነው” ብሏል (መዝ. 35 ፥ 11)። በመቀጠልም “አቤቱ የፊትህ ብርሃን በላያችን ታወቀ በልባችን ደስታን ጨመርህ ፤ ከስንዴ ፍሬና ከወይን ዘይትም ይልቅ በዛ በአንተ የሚታመኑት ሁሉ ለዘለዓለሙ ደስ ይላቸዋል” (መዝ. 4 ፥ 7 ፣ መዝ. 5 ፥ 11)፡፡ በማለት ቅዱስ መጽሐፋችን መንፈሳዊ አስደሳችነትን በተደጋጋሚ ገልጿል፡፡ መልአኩም እንዲህ አለ እነሆ ለእናንተ ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን ታላቅ የምስራች እነግራችኋለሁ አትፍሩ” (ሉቃ. 2 ፥ 10)፡፡ ሕዝቡም ሁሉ ቃለ ወንጌልን ሲሰሙ ፈጽሞ ደስ እንዳላቸው ቅዱስ ማርቆስ እንዲህ ሲል ጽፎልናል ሕዝቡም ደስ ብሎአቸው ያዳምጡት ነበር” (ማር. 12 ፥ 37)። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የወንጌልን አስደሳችነት ምድራዊና ጊዜያዊ ብቻ አለመሆኑን ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ሲል አስረድቶአቸዋል ነገር ግን አጋንንት (መናፍስት) ስለተገዙላችሁ ደስ አይበላችሁ ግን ስማችሁ በመንግሥተ ሰማያት ስለተጻፍ ደስ ይበላችሁ” (ሉቃ. 10 ፥ 20)፡፡ ሕገ ወንጌልን ጠብቀውና በታማኝነት የሚኖሩ ሁሉ ወደ ዘለዓለም ደስታ እንደሚገቡም እንዲህ ሲል አስተምሯል ጌታውም መልካም አንተ የታመንህ በጎ አገልጋይ ፤ በጥቂቱ የታመንህ ስለሆንክ በብዙ እሾምሃለሁ ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው” (ማቴ. 25 ፥ 21)፡፡

ወስበሐት ለእግዚአብሔር፤ ወለወላዲቱ ድንግል፤ ወለመስቀሉ ክቡር

 

የዓመታዊው ቅዱስ ገብርኤል በዓል መርሐ ግብር

Kidame Ehud

የበዓል ማስታወቂያዎች

ሐምሌ 17 ቀን 2008 ዓ. ም. (July 24 / 2016) የሚከበረውን ዓመታዊ የቅዱስ ገብርኤል በዓል ምክንያት በማድረግ በዋዜማው ቅዳሜ ሐምሌ 16 ቀን 2008 ዓ. ም. (July 23 / 2016) ከሰዓት በኋላ ጀምሮ በተጋባዥ መምህራንና ካህናት አባቶች ቤርሾዳለን 44 በሚገኘው ቤተ ክርስቲያናችን የሁለት ቀን መንፈሳዊ ጉባኤ ይደረጋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በዓሉ ሌሊቱን በማኅሌት፣ ጧት በቅዳሴ፣ በዝማሬ፣ በትምህርተ ወንጌልና በሥርዓተ ንግሥ የሚከበር ሲሆን በዕለቱ ሥርዓተ ጋብቻ የሚፈጽሙትን ሙሽሮች የተመለከተ ልዩ መንፈሳዊ መርሐ ግብር የሚኖር ይሆናል፡፡

ስለዚህ ይኸንን መንፈሳዊ መልእክት የምታደምጡ ወገኖች ሁሉ ካላይ በተጠቀሰው ቀንና ሰዓት በቦታው ተገኝታችሁ የጉባኤውና የዚህ ታላቅ መንፈሳዊ በዓል በረከት ተሳታፊ ትሆኑ ዘንድ በእግዚአብሔር ስም ተጋብዛችኋል፡፡

እንዲሁም ቅዱስ ገብርኤል በሚውልበት ዕለት ማለትም ሐምሌ 19 ቀን 2008 ዓ. ም. (July 26 / 2016) ማክሰኞ ጧት ከ8፡00 ሰዓት ጀምሮ የቅዳሴ መርሐ ግብር የሚኖር መሆኑን ከወዲሁ እንገልጻለን፡፡

እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡

Kidame Ehud