መጽናናት-ክፍል ፩

መቼም ሰው ማኅበራዊ እንሰሳ ነው ሲባል ሰምታቹህ ይሆናል። ማኅበራዊ የሚለው ጥሩ ገላጭ ቃል ሚዛኑን ያስተካክለዋል እንጂ ሰውን አንሰሳ ማለት የሚከብድ ይመስላል። በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ሰው ለሰው ምን ያህል ጉልህ ተጽእኖ እንዳለው የተሰወረ አይደለም። እስኪ በዚህ መነሻነት ብዙ ኃሳቦችን መዳሰስ ቢቻልም ስለ መጽናናት ብናወጋስ? ምክንያቱም መንፈሳዊ መጽናናት፣ ከያለንበት ማንኛውም አመልካከት ከፍ ወዳለ መልካም ደረጃ ይመራናልና። ይህ ርዕስ ሰፊ ቢሆንም በየጊዜው በትንሽ በትንሹ እናዳብረዋለን።

በመንፈሳዊ ዕይታ፣ መጽናናት በአንድም ይሁን በሌላ ከራሳችን ውጪ ከተጨማሪ አካል ጋራ ይገናኛል። እንዲሁም መጽናናት እንደተመልካቹ የአመለካከት ሁኔታ ይወሰናል። ለመነሻነት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው ፪ኛ መልእክቱ ምዕራፍ ፯ ቁጥር ፮ (7፥6) ላይ ስንመለከት እንዲህ ይላል፡ ነገር ግን ኀዘንተኞችን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናን”። እዚህ ላይ የምንመለከተው ፣ ዋናው አጽናኝ አምላካችን እግዚአብሔር ሲሆን ፣ ቲቶ ደግሞ የአምላክ መልካምነቱ መገለጫ ሆነ ማለት ነው።

አምላክ በሰዎች በመገለጥ መልካሙን ሲተገብር አስቀድመን አምላክን በማመስገን ቀጥለን ደግሞ የመልካም ምግባር ተመራጭ እና ተግባሪ የሆነውን ሰው እናመሰግንበታለን፥ እንመርቃለን፥ መልካም እንመኝለታለን። በተጨማሪም በሐሳባችን፥ ትካዜያችን፥ ደስታችን፥ ትሕትናችን፥ ምኞታችን በአጠቃላይ አመለካከታችን በሚታየው ነገር ላይ ብቻ ሳይሆን በማይታየው የመልካም ነገሮች ምንጭ ወደ ሆነው አምላክ ዞሮ የሚገጥም ከሆነ፤ በኃዘንም ውስጥ ከአምላክ ጋር ፈገግታ፣ በደስታም ውስጥ በተረጋጋ የሐሴት ፈገግታ በመሆን አምልኮታችንን እናጠናክርበታለን።

መንፈስ ቅዱስ የመራው ጳውሎስ፣ በአለማዊ ዓይኑ የቲቶን መምጣት ተመልክቶ ሳያበቃ፣ በመንፈሳዊው ዓይኑ የእግዚአብሔርን ስራ ተመለከተ። እኛም በምድራዊ ዓይናችን ላይ ብቻ ሳንገደብ፣ ከምናየው ጀርባ ሊኖሩ በሚችሉ መልካም አቅጣጫዎች ብናተኩር ገንቢ ነው። ለማዘንማ እጅግ ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ፣ ጳውሎስ ያልጎበኙትን በማሰብ መማረር በቻለ። ግን ለምን? የሚያመሰግንበት ጥቂት ምክንያት እያለው ስለምን በሚከፋበት ሰፊ ጉድለት ላይ ይመሰጥ? እኛስ በሕይወታችን ውስጥ በሰዎች በኩል የተካፈልናቸው መረዳቶች፥ መታገዞች፥ መረጋጋቶች፥ ኃሳብ መካፈሎች፥ አቅጣጫ ጥቆማዎች፥ ፈገግታዎች፥ ድጋፎች እና የመሳሰሉትን በልባችን በማቆየት የሚያጋጥሙንን መልካም ያልሆኑ ክንዋኔዎች ብንወጣበትስ? መጎዳታችን ወደ ተሻለ አቅጣጫ እንድናቀና የመንቂያና መትጊያ ተነሳሽነት መጨመሪያ እንጂ፤ መማረር ፥ ብስጨት፥ ሀዘን፥ ወቀሳ የመሳሰሉትን፣ የበለጠ መከፋትን የሚያላብሱ እንዳይሆኑብን፣ ከዚህ የጳውሎስ ቃል እንገነዘባለን።

ጽሑፉ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይቀጥላል።

ስብሐት ለእግዚአብሔር።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *