ምኞትና ምስጋና

እንኳን ለበዓለ መድኃኔዓለም አደረሳችሁ።

የእግዚአብሔር ትዕግስት” ከሚለው መጽሐፍ ምዕራፍ አራት ላይ የተወሰደ ጽሑፍ እናካፍላቹ።

ሙሉ እግር የሌለው አንድ ሰው እጅግ ያማረ ለምለም መስክ አይቶ ቁጭ አለና፦ “አይ ይሄ መስክ በእግር እየተራመዱ ቢያቋርጡት እንዴት መልካም ነበር?” ብሎ ተመኘ። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ሌላ እግረኛ መጣና፦ “አይ ይሄ መስክ በፈረስ እየጋለቡ ቢያቋርጡት እንዴት መልካም ነበር?” አለ። ይህን ያዳመጠው የመጀመርያው ወገን፦ “አይ አንተ እግዚአብሔር፣ ማን ነው ባለው የሚያመሰግንህ?” አለ ይባላል።

መጽሐፉን እንዲያነቡት እየጋበዝን፣ መልካሙን ሁሉ መመኘት መልካም ቢሆንም ባለን ማመስገንን ደግሞ የበለጠ መልካም ነው እንላለን። ስለዚህ መመኘት፣ የሀዘን ስሜትን እንዲፈጥርብን ሳይሆን፣ ያለንን ነገር አስተውለን፦ “መድኃኔዓለም፡ ያደረክልኝ እኮ ይበልጣል” ብለን በማመስገን አካላችንን እና መንፈሳችንን በፈገግታ ልናደምቀው ይገባል እንላለን። እስኪ ከመጽሐፍ ቅዱሳችን ተዛማች የሆነ ጥቅስ ቃል በቃል በማቅረብ እንጨርስ፦

“በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና። ማንም ሲፈተን። በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም። ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል። ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች። የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ አትሳቱ።” የያዕቆብ መልእክት ምዕራፍ ፩፥፲፪-፲፮ (1፥12-16)

ምስጋና ይሁን ለአብ፥ ለወልድ፥ ለመንፈስ ቅዱስ፥ አንድ አምላክ ዛሬም፥ ዘወትርም፥ ለዘለዓለም። አሜን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *