የሃሎዊን በዓል

ከተለያዩ መንፈሳዊ ድረ ገጾች የተውጣጣ

የዘመኑ ስልጣኔ በጣም ብዙ በጐ ነገሮች እንዳሉት ሁሉ በተቃራኒውም ትውልዱ የእግዚአብሔር የሆነውን ሁሉ እንዲቃውምና እንዲጠላ ከማድረግ ባሻገር በብዙ የሰይጣን ፍላጻ የተወጋ እንዲሆን አድርጎታል።

የሰይጣንን ክፋት የሚገልጠው የእግዚአብሔር መጽሐፍ ቅዱስ ተዘግቶ የሰይጣን መጽሐፍና የተለያዩ የሰማዩን መንግሥት የሚቃወሙ ጽሑፎችና ፊልሞች በፍጥነት ወደ ትወልዱ እየተሰራጩ ይገኛሉ። በዚህም በሽታ አፍሪካን እና የተለያዩ ዓለማትን ጨምሮ በተለይ በምዕራቡ ዓለም ባሉ ትልልቅ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የሚማሩ ተማሪዎች በግልጽ ተነድፈዋል። ለዚህም ማለማመጃ ካደረጋቸው በርካታ መንገዶች አንዱ  በምዕራባውያኑ ሃሎዊን ተብሎ የሚጠራው በዓል ነው።

ሃሎዊን October 31 ቀን የሚከበር በዓል ሲሆን ኖቬምበር 1 ቀን ደግሞ የሁሉም ቅዱሳን ቀን ወይም በእንግሊዝኛው “All Hallow’s Day” ተብሎ በዘመናት ሰማዕታት የሆኑ ቅዱሳን ይከበሩ ነበር፡፡ ከዚህ ቀን በፊት ያለው የዋዜማ ቀን – October 31 የቅዱሳን ዋዜማ ቀን ወይም በእንግሊዝኛው “All Hallow’s Eve” እየተባለ ሲጠራ ቆይቶ ሰብሰብ፣ አጠር ተደረገና “Hallow-e’en,” ከዚያም በመጨረሻ “Halloween” ተባለ፡፡

የሃሎዊን አጀማመር

አሁን አየርላንድን፣ እንግሊዝን እና ሰሜን ፈረንሳይን በሚያካልለው ስፍራ ከመካከለኛው ዘመን በፊት ይኖር የነበረ “ሴልቲክ” የሚባል ሕዝብ ነበር፡፡ እነዚህ ሕዝቦች (ሴልቲኮች) ወቅቶቻቸው የሚቀያየሩት – በጋው አብቅቶ በሞት በሚመሰለው የክረምት ወራት የሚተካው ኦክቶበር 31 ነበር፡፡ በሴልቲኮች እምነት ወራቶቹ ሲቀያየሩና ብርሃን በጨለማ ሲተካ ኦክቶበር 31 ቀን የሕያዋን ምድርም ሆነ የሙታን ምድር በብዥታ የተሞላ ይሆናል፤ ሙታንም ነፍሳትን ለመጎብኘት ወደዚህ የሕያዋን ምድር ይፈልሳሉ፡፡ ታዲያ እነዚህ የሙታን መናፍስት ጉብኝታቸውን ሲያደርጉ ለመደበቅና ላለመታወቅ የሚፈልጉት ሴልቲኮች ጭምብል (ማስክ) በማድረግና ራሳቸውን በመቀየር ለማምለጥ ሙከራ ያደርጉ ነበር፡፡

ሌላው በዚህ የወቅት መለወጫ ጊዜ “የብርሃን ዘመን” መጠናቀቁን ለማወጅና መናፍስቱ ከመጪው የክረምት ወራት ሕዝቡን እንዲታደጉ፤ ጭለማው የክረምት ጊዜያት የበራ እንዲሆን በመመኘት የችቦ ደመራ ያበሩ ነበር፡፡ በዚህም ምሽት በርካታ ጥንቆላ፣ ከአጋንንት የመነጋገር ተግባራትም ይፈጸማሉ፡፡ ሰዎች የሞቱባቸውን ዘመዶቻቸውን በመናፍስቱ አማካኝነት ይጠራሉ፤ መጪው የሰብል ዘመን ምን እንደሚሆን ይጠይቃሉ/ያስጠነቁላሉ፤ . . . ሌሎችም እጅግ በርካታ መናፍስትን የመጥራትና ከአጋንንት ጋር የመገናኘት ተግባራት ይከናውኑ ነበር፡፡

የእግዚአብሔር ቃል ግን እንዲህ ይላል፡- “ወደ መናፍስት ጠሪዎችና ወደ ጠንቋዮች አትሂዱ፤ እንዳትረክሱባቸውም አትፈልጉአቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ”። (ዘሌዋ. 19 : 31)

“ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ ጽድቅ ከአመጽ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና ብርሃንም ከጨላማ ጋር ምን ኅብረት አለው?” (2 ቆሮ. 6 ፡ 14)

“ነገር ግን አሕዛብ የሚሠዉት ለአጋንንት እንዲሆን እንጂ ለእግዚአብሔር እንዳይሠዉ እላለሁ፤ ከአጋንንትም ጋር ማኅበረተኞች እንድትሆኑ አልወድም። የጌታን ጽዋና የአጋንንትን ጽዋ ልትጠጡ አትችሉም፤ ከጌታ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ ልትካፈሉ አትችሉም”። (1 ቆሮ. 10 : 20 – 21)

ይህ በዓል በአሜሪካ የጀመረው በ19ኛው  መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ሲሆን  ይህም ወደ አሜሪካ በስደት በገቡት የአይርሽ ተወላጆች  እንደሆነ ይነገራል። ባሁኑ ጊዜ በዓሉ በአሜሪካ ብዙ ሚሊየን ዶላር ገቢ የሚያስገባ በዓል ስለሆነ ምንም ይሁን ምን በዓሉ ከፍተኛ ተወዳጅነት እንዲኖረው አድርጐታል።

ዲያብሎስም የራሱን አስተሳሰብና ክፉ እሴቶች በጠቅላላ በሕዝቡ ላይ የሚዘረግፍበት ቀን ስለሆነ የመንፈሱ ሚና የተለየ ነው።

ይኽ ቀን ዲያብሎስ ልዩ ግብር የሚቀበልበትና ለነገው የሰይጣኒዝም አምሎኮ ሥነ ሥርዓት የሚንበረከኩ ልጆችን ማፍሪያና ማለማመጃ ከመሆኑም በላይ መሥዋዕት የሚቀበልበት ትልቁ መንገድ እየሆነ ከመጣ ጊዜያቶች ተቆጥረዋል።

የሰይጣንን አስከፊ ገጽታዎች ለማሳየት የተፈበረኩት እቃዎች የሚሸጡበት ሥፍራ በራሱ፤ የሙታንን መንፈስና፤ የተለያዩ የሙታን አፅም፤ እንዲሁም በጣም ዘግናኝ የሆኑ የእንስሳትና የአራዊት ምስሎች፤ የበሰበሱና የፈረሱ የሰው አካል ጉርድራጅ የሆኑ ምስሎች፤ እንዲሁም ነፍስ አለው የተባለውን ሁሉ ከሰው ጀምሮ አስቃይቶ እና አስጨንቆ የሚገድሉ የስለት መሳሪያዎች ምስል፤ በተጨማሪም ለዓይን እይታ የሚቀፉ ልብሶችና አሸንጉሊቶች ተደርድሮ ለተመለከተ በቀጥታ የሰይጣን ዓለም /ሰፈር / ውስጥ እንደገባ አድርጎ እንዲያስብ ያስገድዳሉ። በዚህም ቀን ሕፃናት የመናፍስቱን ልብስና የአጋንንትንና የሙት መንፈስን ኃይል የሚገልጡ ልብሶችን ለብሰው በቀን  በማታ እንዲንቀሳቀሱ ያደርጋሉ።

አስገራሚው ግን በዚህ ቀን ከእናት ከአባታቸው እጅ ባልታወቀ መንገድ የሚሰረቁ ልጆች እና ከቤተሰባቸው ተለይተው የሚጠፉ ቤተሰቦች ቁጥር ነው።

በዚህ ዕለት የሚለበሱትና የሚጌጥባቸው ቁሳቁሶች በአጠቃላይ ዛሬ የሰይጣኒዝም እምነት ተከታዮች ዘንድ በቤተ አምልኳቸው የሚለብሱትና የሚያጌጡበት፤ አምልኳቸውን የሚፈጹመበት ቁሳቁስ ነው። ታድያ ዛሬ በሕፃንኑቱ በሃሎዊን ምክንያት እነዚህን ነገሮች ገንዘቡ እንዲያደርጋቸው የተገፋ ሕፃን ነገ የሰይጣንን እምነት ተግባራዊ እንዲያደርግ ቢጠየቅ ለእርሱ ምንም አዲስ ነገር አይኖርም፡፡ ለሰይጣኒዝም አስተሳሰብና እግዚብሔር የለም ለሚለው ክፉ የፍልስፍና እብደትም በር ከፋች ይሆናል።

በአጠቃላይ ይህ ቀን የጨለማው ገዢ ተከብሮ የሚውልበት ዕለት ስለሆነ እግዚአብሔርን ለሚያመልኩ ቤተሰቦች የማይመችና የጨለማ ቀን ነው።

በመጨረሻም በውጪው ዓለም የሚኖር ቤተሰብ ለልጆቹ ቢያደርግ ተብሎ ከሚታሰቡት ጥቂቶቹ፡-

ልጆችን በፍቅርና በትሕትና ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲያውቁና የመቅደሱ የፍቅር ሽታ እንዲሸታቸው ማድረግና በሄዱበት ዕለት ብርቱ ማበረታቻ ማበርከት፤

የእግዚአብሔርን ፍቅር እንደ ሙሴ እናት በልባቸው እንዲቀረጽ ማድረግ፤

ዓለሙን እያመሰ ያለው ክፉ መንፈስ ማን እንደሆነ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ፤

ልጅነታቸውን የመጠነ ምክር ዕለት ዕለት ከመስጠት ጋር እግዚአብሔርም ስለ ሕፃናት ያለውን ከፍተኛ ፍቅር ማስረዳት፤ . . .

በዚህ ዕለት እንደ ልጆች መሆን አለብን ብለው በጓደኞቻቸው ጫና የሚያስቸግሩ ሕፃናት ካሉ ደግሞ የሙት መንፈስን የሚገልጥ ልብስ ሳይሆን ትክክለኛውን መልአክ የሚገልጥ ብርሃናማ ልብሶችን እንዲመርጡ በፍቅር ማስረዳት፤

ሲሆን ሲሆን በዓሉ የሌሎች እንደሆነ በመግለጥ የቤተ ክርስቲያን በዓላት በሚከበሩበት ጊዜ ፍላጎታቸውን ለማድረግ ቃል በመግባት ውስጣቸው እንዲያምን ማድረግ።

እነ ነቢዩ ዳንኤል እና ሦስቱ ወጣቶች አናንያ፤ አዛርያ፤ ሚሳኤል በባቢሎን ምድር ባቢሎናውያን የሚያደርጉትን የጣዖት አምልኮን መቃወም ብቻ ሳይሆን ልብንና መንፈስን ከሚያበላሽ አመጋገብ ራሳቸውን ይጠብቁ እንደነበረና እግዚአብሔርም ከጠንቋዮችና ከሌሎች ይልቅ እንዴት እንዳከበራቸው በሚደርስባቸው ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ረዳታቸው እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እንዲሁም የነ ዮሴፍን ታሪክ በባዕድ ምድር እግዚአብሔር ምን እንደሠራላቸው ቤተሰብ እንዚህንና መልካም የቅዱስ መጽሐፍ ታሪኮችን ለልጆች ማስረዳት ይጠቅማል።

እግዚአብሔር ልጆቻችንን ከአውሬው መንፈስ ይጠብቅልን፡፡ አሜን!!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *