የሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ታሪክ በአጭሩ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰማዕት በፍልስጤም ግዛት ልዩ ስሙ ልዳ በሚባል አገር በ፫ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ተወለደ፡፡

አሥር ዓመት ሲሆነው አባቱ አረፈ፡፡ እሱም በዘመኑ የነበረውን ትምህርት ማለትም ፈረስ መጋለብ፤ ጦር ውርወራና ጋሻ መመከት እየተማረ አደገ፡፡ ሃያ ዓመት ሲሞላው ፲፭ ዓመት ከሆናት የንጉሥ ልጅ ጋር ሊያጋቡት ቢሞክሩም እግዚአብሔር ለልዩ አገልግሎት መርጦታልና የጋብቻ ጥያቄውን አልቀበልም በማለት ስለእምነቱ እየመሰከረ ፈጣሪውን ማገልገል ጀመረ። ”በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፡፡” እንዲል (ማቴ. ፲፥፴፪)

የቤይሩት (የሊባኖስ) ሰዎች ደራጎንን እያመልኩ ሴት ልጃቸውን ይገብሩለት ነበር፡፡ ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስም ቤይሩታዊቷን ወጣት ታድጎ/አድኖ ደራጎኑን በበትረ መስቀሉ ድል በማድረግ ገድሎታል፡፡በፋርስ (በኢራን) ዱድያኖስ የተባለ ንጉሥ ሰባ ነገሥታትን እየሰበሰበ ለሰባ ጣዖታት ሲሰግድና ሲያሰግድ ይኖር ነበር፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰማዕትም እንደ ኤልያስ ለእምነቱ ቀንቶ ንጉሡን መገሰጽ ጀመረ፡፡“ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ።” እንዲል፡፡ (ማቴ. ፲፥፳፰)
ለሰባት ዓመታት ያህል ልዩ ልዩ መከራን እየተቀበለ በጽኑዕ ተጋድሎ ከኖረ በኋላ ሚያዝያ ፳፫ ቀን በ፳፯ ዓመቱ ሰማዕትነትን ተቀብሎ አርፏል፡፡

የሰማዕቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ በረከትና ረድኤት አይለየን፤ ለእርሱ የሰጠውን የእምነት ጽናትና ብርታት ለእኛም ያድለን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *